ደወለችልኝ አከታትላ ቢጨንቃት፣
ፋታ ላትሰጠኝ በለሊት።
አንድ ጊዜ ያዝልኝ ፣
ሌላ ጥሪ መጣብኝ ፣
አልኩና የድንገተኛ ክፍል ሀኪሙን፣
አነሳሁላት ስልኩን።
“ዶክተር ነኘ፣ ከፅኑ ህሙማን፣
የደሟ ጨው በጣም ዝቅ ያለ ታማሚ አለችን፣
ያንተን እርዳታ እንፈልጋለን ።”
አለች …ቶሎ ቶሎ እየተነፈሰች።
ለመሆኑ ስንት ቢሆን ነው ?
የጨው ማነስ ክፋት አለው።
“ዘጠና ዘጠኝ “
በሊትር?
ነው ያልሽው ዶክተር?
እንደዚህም ያነሰ አላየሁ።
“ምኑንም አታዉቀው
ያመጣት ባሏ ነው”
በእኩለ ሌሊት፣
በዌስተን ከተማ ፣ፍሎሪዳ ግዛት፣
ነጩን የሆስፒታል ጋዉን፣
ከመኪናዬ ዃላወንበር ፣
አንገቴላይ ጣል አርጌ፣
የልብ ማዳመጫውን፣
የደሟን ጨው ላስተካክል፣
እየተማፀንኩ ወላዲትን፣
ደረስኩ…እየከነፍኩ!
ማሪያ ፣ ማሪያ
ማሪያ ፎልች?
አይኗን እንደከደነች ፣
እጆቿን አንቀሳቀሰች።
የተከማቸ ጨው ፣
የያዘውን የፈሳሽ ቀመር፣
በልክ በልኩ፣
ሰጠናት በደምስር ።
ጠጥታ ኖሯል ፣ብዙ ፈሳሽ
ከውሀው፣ ከጭማቂው
ከሻይና ከቡናው።
አዋቂ ነኝ ባይ ልጅት፣
መጥታ ከሌላ ግዛት፣
ለኩላሊት ጥሩ ነው መጠጣት፣
ብላ… ፈሳሹን ሁሉ ብታግታት
የደሟ ጨው ከመቶ አርባ ፤
አሽቆለቆለ እያዋዛት።
መጀመሪያ ድንግዝግዝ ፣
ማቅለሽለሽ ማስመለስ፣
ከዛ ማ ምኑን አውቃው።
በልክ በልኩ በቀስታ፣
እንዳይነፍር ጭንቅላቷ፣
ገድበን በቀን ከስምንት ፣
ከዘጠናዘጠኝ …መቶ ሰባት፣
ከዛም መቶ አስራ አራት ፣
አስተካከልነው የጨው መጠኗን፣
አምስት ቀን ፈጅቶብን፣
አማላጅ ይዘን ወላዲትን።
ዉሀም ይወስዳል ፣ በልኩ ካልሆነ፣
እያንገዛገዘ ፣ እያጥወለወለ።
ሱራፌል
( severe hyponatremia, ከሆስፒታል ገጠመኞቼ)